ዘላለም
Zelalem
5:55 · አማርኛ
ቁጥር 1 · Verse 1
በእጅ ብልጫ አልተሾምክ፤ ድምፅም አይሽርህም
ዘመን አላመጣህ፤ ወቅት አያልፍብህም
ካንተ ሚበልጥ መጥቶ ስፍራህን አትለቅም
ሁልጊዜ፣ ለዘላለም ‘ሚለካካህ የለም
ስትዘረጋ ሰማይ ስትመሠርት ምድር
ማን አብሮህ ነበረ? ማን ለገሰህ ምክር?
ከማን ተረከብከው ዙፋን መንበርህን?
ሿሚ ሻሪ የለው ሥርወ-መንግሥትህ!
ከማን ደም ተቃብተህ ዘውድን አጽንተሃል?
የማንን ጦር ፈርተህ አዎ ጠባቂ አኑረሃል?
ዙፋንህ መሠረት በጽድቅ ነው ፍርድህ
በትርህ የቅንነት አዎ ሰላም፣ ፍትሕ፣ ርትዕ
አዝማች · Chorus
ኧረ እንዳንተ ያለ አልነበረም!
ዛሬም የለም አይኖርም ዘላለም!
ቁጥር 2 · Verse 2
ዘመንህን ሽበት ሞት አይገላምጠው፣
ዙፋንህ ተተኪ ዐልጋ ወራሽ የለው፣
ንጉሥ በብርታትህ ያለህ በዐምባህ፣
ያላንዳች ምክትል ዘላለም ‘ገዢ ነህ
አለሁ የሚል ማነው ከኋላ ከፊትህ?
አንተ ያው አንተ ነህ፤ አዎ አያልቁ ዓመታትህ፤
ፀሐይ አትጠልቅብህ የለህም ትናንት፤
አትናፍቅ ነገን ሺ ዓመት አንድ ቀን ነው ፊትህ
አዝማች · Chorus
ኧረ እንዳንተ ያለ አልነበረም!
ዛሬም የለም አይኖርም ዘላለም!
ቁጥር 3 · Verse 3
ለማን ልትገብር ለዋስትናህ?
ሁሉን መጋቢ ከእጆችህ!
ቃልህ ፈጣሪ፣ እስትንፋስህ አኗሪ
ሁሉን በፈርጁ አስተዳዳሪ
ዕውቀት ገንዘብህ ጥበብ መዝገብህ
ማስተዋል ካባህ እውነት ምግባርህ
በሰማይ ምድር ‘ሚመስልህ የለም
ሁሉን ይገዛል መንግስትህ ዘላለም
ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው፣
ክብር፣ ምስጋና፣ ሞገስ፣ ኀይል የአንተ ነው
ምንጭ፦ ግጥሙ በ WikiMezmur ማኅበረሰብ የተገለበጠ ነው። የግጥሙ መብት የደራሲው ነው — የመብት ጥያቄ